arrow-left-dark
Back

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በትብብር እና በቀጣናዊ ሁነቶች ዙሪያ ተወያዩ

Dot
13 ማርች 2026
|
አቡዳቢ

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት በልዑል ሼክ ሙሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን እና የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ በሁለትዮሽ ትብብር፣ በተለይም በኢኮኖሚ፣ በንግድ እና በልማት ዘርፎች፣ እንዲሁም የሁለቱን ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮችና የጋራ ጥቅሞች በሚደግፍ እና ለህዝቦቻቸው ብልጽግናን በሚያመጣ መልኩ ግንኙነታቸውን ማሳደግ በሚቻልባቸው እድሎች ዙሪያ ተወያይተዋል።

 

ውይይቱ የተካሄደው በኤምሬትስ የሥራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ከሚገኙት ከክቡር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ልዑልነታቸው ባደረጉት ስብሰባ ወቅት ነው።

 

ስብሰባው በተጨማሪም በግጭቶች መባባስ ምክንያት በመካከለኛው ምስራቅ እየታዩ ያሉ ሁነቶችን እና በቀጣናዊ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደህንነትና መረጋጋት ላይ የሚያሳድሩትን አደገኛ ተጽእኖ ዳስሷል። በዚህም ረገድ ክቡር ዶክተር አብይ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና በሌሎች የቀጣናው ሀገራት ላይ እየደረሰ ያለውን ግልጽ የኢራን ጥቃት ያወገዙ ሲሆን፣ ጥቃቶቹ የሀገራትን ሉአላዊነት እና የዓለም አቀፍ ህግን የሚጥሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ደህንነቷን፣ የግዛት አንድነቷን እና የህዝቧን ሰላም ለመጠበቅ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከምትወስዳቸው እርምጃዎች ሁሉ ጎን የምትቆም መሆኗን አረጋግጠዋል።

 

ልዑልነታቸው ኢትዮጵያ ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ላሳየችው የደገፋ አቋም ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

 

ልዑልነታቸው በደቡብ ኢትዮጵያ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በተከሰተው የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ለኢትዮጵያ ህዝብ የተሰማቸውን የጠለቀ ሐዘን የገለጹ ሲሆን፣ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከኢትዮጵያ ጎን የምትቆም መሆኗንም አረጋግጠዋል።

 

ሁለቱ ወገኖች ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆም አጽንኦት የሰጡ ሲሆን፣ ተጨማሪ ውጥረቶችንና ቀውሶችን በሚከላከል እንዲሁም የቀጣናውን ደህንነትና መረጋጋት በሚጠብቅ መልኩ በቀጣናው ያሉ ያልተፈቱ ጉዳዮችን ለመፍታት የሚያስችል ጥልቅ ውይይትና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።

Also-Available
1 / 2