arrow-left-dark
Back

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት በCOP28 ከየልዑካን ቡድኖቹ መሪዎች ጋር ተወያዩ

Dot
30 ኖቬምበር 2023
|
አቡዳቢ

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት ልዑል ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ዛሬ በኤክስፖ ሲቲ ዱባይ መካሄድ በጀመረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ (COP28) ጎን ለጎን ከፓራጓይ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ክቡር ሳንቲያጎ ፔኛ፣ ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እና ከቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ልዩ መልዕክተኛ ከክቡር ዴንግ ሲጁን ጋር በተናጠል ተወያይተዋል።

ልዑልነታቸው ከእንግዶቻቸው ጋር በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና በየሀገሮቻቸው መካከል ባለው የሁለትዮሽ ግንኙነት፣ እንዲሁም በጋራ ትኩረት በሚሹ ክልላዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። በተጨማሪም ውይይቶቹ ትኩረታቸውን በCOP28 እና ለሁሉም ሀገራት ጠቃሚ የሆነውን የአየር ንብረት እርምጃ ለማጠናከር የሚያስችሉ ውጤታማ ውሳኔዎች ላይ ለመድረስ በተሳታፊዎች መካከል ባለው ትብብር እና የጋራ እንቅስቃሴ አስፈላጊነት ላይ አድርገዋል።

በስብሰባዎቹ ላይ የምክትል ፕሬዝዳንት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ምስክትል እና የፕሬዝዳንታዊ ፍርድ ቤት ሚኒስትር ልዑል ሼክ መንሱር ቢን ዛይድ አል ናህያን፤ ልዑል ሼክ ሃምዳን ቢን ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን፤ በፕሬዝዳንታዊ ፍርድ ቤት የልዩ ጉዳዮች አማካሪ ክቡር ሼክ ሞሃመድ ቢን ሃማድ ቢን ታህኑን አል ናህያን፤ የዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ክብርት ሪም ቢንት ኢብራሂም አል ሀሺሚ፤ በአሜሪካ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አምባሳደር ክቡር የሱፍ አል ኦታይባ እና ሚኒስትሮችንና ከፍተኛ ባለስልጣናትን ያካተቱት የእንግዳ ሀገራቱ አጃቢ ልዑካን ቡድኖች ተገኝተዋል።

ልዑልነታቸው ፕሬዝዳንቱ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ ትግበራ፣ የታዳሽ ኃይል ልማት እና በሌሎች የዘላቂነት ጥረቶች ዙሪያ ያላትን ተሞክሮ ያቀረበችበትን በCOP28 የሚገኘውን የኢትዮጵያ ፓቪሊዮን (የኤግዚቢሽን ስፍራ) ጎብኝተዋል።

Also-Available
1 / 3